አንተ ባለ አደራ፤ ችቦው የዕውቀት ጎተራ፣
የብልፅግና መሠረት፤ የሙያዎች ሁሉ አውራ።
የመበልፀጊያ ጎዳና፤የኢኮኖሚው ማገር፣
ራዕዬ ብዙ ነህና ፤ የዛሬው አንተ መምህር ።
ሻማ ሆነህ ብትነድም፤ ለሌሎች የምታበራ፣
አገር የሁሉ ብትሆንም፤የምትለማ በጋራ፣
ኢትዮጵያ እንድቶን ቀዳሚ፤ እንደ ብረት ጠንካራ።
ያንተ ጥረት ያሻታል፤ ነህና የዕውቀት መሀንድስ፣
የሰውን አዕምሮ በማለምለም፤ ሁልጊዜ የምታድስ።
ብርቱ ዜጋ ፈጣሪ፤ ነህና የዕውቀት ማሽን፣
ፀረ-ድህነት ነህና፤ ልመናን የምትረሽን።
የዕውቀት አባት ነህና፤ አደራ ያለብህ ሙህር፣
ታጠቅና ተነሳ፤ አንተ የዛሬ መምህር።
ሐኪም፣ኢንጅነር ቢመጣ፤ ጠፈር ላይም ቢወጣ፣
ቢሆንም ጎበዝ ተማሪ፤ አራት ነጥብ ቢያመጣ፣
ያለ አንተ አይሆንምና፤ ግደታህን ተወጣ፣
ፖለቲካ ያወቀ፤ ያገር መሪ ቢመጣ፣
አዲስ ግኝት ቀማሪ፤ ጥሩ ኬሚስት ቢመጣ።
ብልፅግና ብናሳይ፤ የዕድገት ዲጂት ቢደረደር፣
ወደ ሰማይ ቢወጣ፤ ምርምር ቢያደርግ በምድር ።
ሁሉም ባንተ ላይ አልፎ ነው፤ ስለሆንከው መሰላል፣
መረማመጃ አሻጋሪ፤ ስለሆንከው ነው በቀላል።
በመድረክ ላይ ቢናገር፤ ሆኖ ቢገኝ ተደማጭ፣
ከፊት ለፊትህ ጉብ ቢል፤ ስልጣን ይዞ ተቀማጭ፣
እውቀትህን አካፍለህ ነው፤ በድብቅ ሳይሆን በግላጭ።
እናማ አንተ መምህር፤ በእውቀት ሁሉንም በላጭ፣
የድህነት መላጫ፤ ነህና ዶርኮ ምላጭ፣
አዲስ እውቀት እንዲያበራ፤ እንዲጠፋ ከምድር እምቦጭ፣
አደራህ ብዙ ነውና፤ ባለ ተስፋ ሁን ሁሉን በላጭ።
ተመራምረህ ዜጋ ፍጠር፤ እምቦጭን የሚያጠፋ፣
አገራችን እንድታድግ፤ እንድናገኝ አዲስ ተስፋ።
ወገብህን አስረህ ተነስ፤ ሞተር ነህና የአገር፣
የሁሉም አንቀሳቃሽ አለኝታ ነህ የአገር ማገር።
አገርህን ታደግ ከጥፋት፤ ሳትከፋፈል በብሔር፣
አንዲነታችን ጠንክሮ፤ እንድንኖር በህብር፣
ሀላፊነቱ ያንተ ነው፤ ዜጎችን በማስተማር።
ይህቺ የጀግኖች አገር ባለቤት፤ በዓለም ከፍ እንድል ሰንደቋ፣
ሳንለያይ በብሔር፤ በሀይማኖት በቋንቋ።
ባለ ራዕይ ነህና፤ እስቲ ገንባ መሰረቷን፣
በዓለም ታሳይ ስልጣኔን፤ የጥንት ማንነቷን።
ቋንቋ ሒሳብ ስነ-ጥበብ፤ ብሎም ሳይንስ ስታስተምር፣
ሆነህ ሞዴል አሳያቸው፤ ስነ-ምግባርን በተግባር፣
እንዲፈጠር ጥሩ ዜጋ፤ አንዱ ሌላውን የሚያከብር።
ውዱ መምህር!፤ የሙያዎች እናት ባለቤት፣
አደራ ይዘህ በልብህ፤ ራዕይህን አድርግ እውነት።
እንደ ተግባርህ ብዛት፤ ባይሰጥህም ክብር፣
ባታገኝም ጥቅማጥቅም፤ ክፍያ ቢያንስህም በብር።
ያንተ ጥቅም እርካታ ነው፤ የአገር እድገቷ ሲያምር።
በመ/ር ያሲን እንድሪስ
