/በረከት በላይነህ/
የተራበ ነብር ከሩቅ ተመልክታ
ሚዳቋ ፀለየች….
“አውጣኝ አውጣኝ” አለች ለፈጠራት ጌታ
…
ነብሩም ተርቦ
ወደ አምላኩ ቀርቦ
ሚዳቆዋን አይቶ – አንጀቱ ከሆዱ እንደተጣበቀ
ፈቅዶ እንዲሰጠው – አምላኩን ጠየቀ
…
የሁላችን ሰሪ
ፀሎታቸውንም ሰማቸው ፈጣሪ
አምላክም በድምፁ ሚዳቆዋን አላት
“ሩጠሽ አምልጪ ከበረታው ጠላት”
…
ነብሩንም አለው – “እሩጥ ተከተላት ምግብ አርገህ ብላት”
ሚዳቆዋ ስትሮጥ
ከነብር ለማምለጥ
ነብሩም ሲከተላት
ሆዱን ሊሞላባት
…
ቋጥኙን ስትዘል እግሯ ተስፈንጥሮ
ሆዱን ብትረግጠው የተኛው ከርከሮ
ከእንቅልፉ ሲነቃ ልክ ሲደነብር
ጉሮሮውን ያዘው የፀለየው ነብር
…
አውጣኝ ያለው ወጥቶ አብላኝ ያለው በላ
ሳይፀልይ ያደረው ከርከሮ ተበላ።